የሪፎርም ለውጡ ድል በብር ለውጥ ድል ይደገማል!

305
9825

ኢኮኖሚያችን ደካማ መነሻ ነው ያለው። የተዛነፉ ሚዛኖችና ከማእቀፍ የወጡ ነገሮች ይዞ ነው የሚንደፋደፈው። ከእጅ ወዳፍ ከመሆን ብዙም ፈቀቅ አላለም። የኑሮ ውድነት የሰማይ ክልል አልፎ ሄዷል። ድሮም በጥንቃቄ ተይዞ እንጂ በቋፍ ላይ የነበረው ኢኮኖሚ አሁን ግልጽ ሸንቆቆ ውስጥ ገብቷል። ስለዚህ የአመራሩ ችግር፣ ለፖለቲካው ችግር፣ እሱ ደግሞ ለጸጥታና ደህንነት ችግር፣ ይኽ ሳይፈታ ወደ ኢኮኖሚ ችግር ሰተት ብለን ገብተናል። አሁን ደግሞ የገንዘብ ህትመት ለውጥ ተከትሎ፣ ሌላ ችግር እየጎተትን ይመስላል። በዚህ ሁሉ በመንግስትና በተቋማት ላይ፣ በህጎችና በአሰራር ላይ እምነት የማጣት ሁኔታ እያንሰራራ መጥቷል። የመንግስትና የፖለቲካ አመራሮች እነዚህን ውስብስብ ችግሮች ላይ አዳዲሶች ሲጨምሩ እንጂ መልክ ሲያስይዙ አይታዩም።

ለምሳሌ ከገንዝብ ለውጥ ጋር ተያይዞ ያለውን እሳቤና የተወሰዱ ተግባራዊ እርምጃዎችን እንመልከት። ሃሳቡ፣ የብሮችን ህትመትና ወረቀታዊ ጥራት ለማስተካከል እና፣ ብዙ ብሮች ከባንኮች ውጭ ስለሆኑ ወደ ባንክ የሚመለሱበትን ሁኔታ ለመፍጠር ነው የሚል ምክንያት ተሰጥቷል። በተጨማሪም፣ ለህገወጥ ተግባራት የሚውሉ ገንዘቦችና በጎሬቤት የተከማቹትን ህገ-ወጥ ብሮች ከጥቅም ውጭ ለማድረግ ነው የሚል ማብራሪያ ይደመጣል። ይኸ ህትመታዊና ወረቀታዊ ጥራት ለማስተካከል የሚለው ምክንያት በራሱ መጥፎ ነው ባይባልም “ይህን ለማድረግ፣ መንግስት የተሻለ ወቅትና ሂደት ነው ወይ የመረጠው?” ቢባል አጥጋቢ መልስ የለም። ይኽ አሁን ያለንበትን የፖለቲካ አለመረጋጋት ከታለፈ በኋላ ለመተግበር፣ ለዚህ የሚሆኑ አገራዊ ግብአቶችንም በሚገባ ለማደራጀት ዕድል በሚሰጥ መልኩ አይደለም የተፈጸመው። እንዲያውም ነገሩ ሁሉ እንዳይቀር እንጂ እንዲያምር ተፈልጎ የተደረገ አይመስልም። ውጤቱም የሚነግረን እውነታ ይኸው ነው። የቢቢሲው ዘገባ እንዲህ ይላል፡ “ቢቢሲ ያነጋገራቸው የብሔራዊ ባንክ የከረንሲ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ አበበ ሰንበቴ ግን አዲሶቹ የብር ኖቶች ላይ የሚታየው ልዩነት ተራ የሕትመት ችግር እንጂ ተመሳስሎ የተሠራ እንዳልሆነ ገልፀዋል።”በአንዲት አገር አዳዲስ ዝቅታዎች እየተመዘገቡ፣ እና ሊያጋጥም እንደሚችል፣ የማያስደነግጥ ስህተት (the new normal” ተደርጎ ሲቆጠር ስህተቱ ራሱ ብቻ ሳይሆን፣ ስህተቱን በድግግሞሽ፣ በሰፋ መልኩና በቀጣይነት እንደሚዘልቅ ያመላክታል።

እንደ እውነቱ ከሆነ የብር ህትመት ዲዛይነር፣ ኤዲተር፣ ፊደል ለቃሚ ወዘተ ሰው መሆን አልነበረበትም። ለእግዚአብሄር ወይም ለሰይጣን ሊሰጥ የሚገባው ሥራ ነው፤ ፍጹምነት (superb meticulosity)  የሚጠይቅ ስለሆነ። ሰይጣንና እግዚአብሄር ለፊደልና ምስል ለቀማ ማምጣት ሰለማይቻል፣ ይህንን ክፍተት ለማካካስ በጣም ብዙ ጠንቃቃ አይኖች፣ ብዙ ጊዜና የቁጥጥር እንዲሁም የልምምድ ሙከራዎች፣ ከሰው አቅም በላይ የሆኑትን ደግሞ በቴክኖሎጂ በመደገፍ ያለምንም ስህተት እንዲታተም ይደረጋል። እንደዛም ሆኖ የተሳሳቱ ህትመቶች ሊሾልኩ ይችላሉ። እነሱን ሰብስቦ ከስርጭት ማውጣት ይገባል። አሜሪካ እሰከ 6% የሚሆኑ ዶላሮች ወረቀቱ በመዛነፉ ምክንያት፣ ወይም በቀለም መብዛት ወይም ማነስ ወዘተ፣ እጅግ ለማየት የሚያዳግቱ ጥቃቅን ዝንፈቶች ያሉባቸው የገንዘብ ህትመቶች ወደ ባንኮችና ሰዎች እንዳይሄዱ ከፍተኛ ቁጥጥር በማድረግ ከጥቅም ውጭ ታደርጋለች። ይህ የሁሉም አገሮች ልምድ ይመስለኛል። ምክንያቱም የአንድ ትውልድ ተመሳሳይ ዋጋ ያላቸው ብሮች (same print generation) በረድፍነት የሚያገለግለው ቁጥራቸው ከመለያየቱ በቀር፣ በመልክ፣ ቅርጽና ምስል ፍጹም አንድ አይነትነት መጋራት አለባቸው። ይህ የገንዘቦች ህትመት መሰረታዊ ውቅር ነው። በሆነ ምክንያት ስህተት ከተፈጠረ ለማረም እንደመሞከር “ምንም አይደለም” ብሎ ለማቻቻል የሚሞክር የብሄራዊ ባንክ ባለስልጣን ማየት አዲሱ የኢትዮጵያ ዝቅታ ነው። አንዱ የኢኮኖሚ የዩኒቨርስቲ ምሁር “እኔ እንኳን የተማሪዎቼ የፈተና ወረቀት ላይ የፊደል ህጸጽ ካየሁ ውጤታቸው ሳልቀንስ አላልፋትም” ሲሉ ብብሩ ህትመት ላይ የታዩት የፊደሎችና ይምስሎች ዝብርቅርቅታ ተችቷል። ስለዚህ “በጥራት ታትሞ የተሻለ መልክና እድሜ ያለው ገንዘብ“ ተብሎ የተቀመጠው ግብ ከሽፏል።

የኢትዮጵያን የመከላከያን ተቋም ከ1.5 ሚልዮን በላይ ካገኘው “ወርሰህ ብላ”  የሚል መገለጫም ተሰጥቷል። ይኽ በተወካዮች ምክር ቤት የወጣ አዋጅ አይደለም። የመከላከያ ሰራዊት ለዚህ ዓይነት ያለተግባ ሥራ ማሰመራትም እጅግ አደገኛ ውሳኔ ነው። ጠሚር አቢይ አህመድ ይህንን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ “ከ1.5 ሚልዮን ብር በላይ የያዘ ሰው automatically void ነው የሚሆነው። ይወረሳል – ገንዘቡ። ይወረሳል፣ መከላከያ ከወረሰው፣ መከላከያን ለማጠናከር እንጠቀምበታለን። ለኛ አይሰጡንም፣ መከላከያ ውረሱትና እናንተ ተጠቀሙበት፣ ራሳቹሁን አጠናክሩበት ገንዘቡ ብለናቸዋል።” ይኽ በጣም አስገራሚ ነው። ገንዘባቹህ ወደ ባንክ አስገቡ ማለት ሲቻል ( ዓላማው cash hording ለመከላከል ከሆነ) የታጠቀን ኃይል በገንዘብ ጉዳይ ላይ እና ዜጎችን በተመለከተ ተለክቶ ያልተሰጠ ልቅ (ፍትሸንም ስለሚጨምር እና አፈጻጸሙም ከልክ እንዳያልፍ የሚገታ ነገር ስለሌለው) ስልጣን መስጠት ጣጣው ዘርፈ ብዙ ነው። ምንጩ ከወንጀል ጋር የተገናኘ ከሆነ፣ የተዘረፈ ወይም የተሰረቀ ገንዘብ ከሆነ፣ ለባለቤቱ ወይም ለመንግስት የሚመለስበት የወንጀልም የፍታብሄርም ህጎች አሉን። ከዚያ ውጭ፣ ሃሽሽ ወይም የውጭ ምንዛሬ ይመስል፣ በካሽ የተገኘ ንብረትና ሃብት ይወረስ የሚል ነገር፣ አንደኛ ምክንያታዊ አይደለም፣ ሁለተኛ መቸ የወጣን ህግ ወይም አዋጅ መሰረት ያደረገ ውሳኔ ነው? እንዲህ አይነት አዋጅ፣ ፓርላማ ካልሆነ ማን ሊያወጣው ይችላል? እንዳልኩት አዋጅ እንኳ ቢኖር ህጋዊነት እንጂ አግባብነት አለው ማለት አይደለም። ግን አሁን ህጋዊም፣ አግባብም አይመስልም።

ሁለተኛ መከላከያ ወደዚህ አይነት ሥራ የሚገባበት ነገር ፈጽሞ ጤናማ አይደለም። መከላከያ ቤት ለቤት እያሰሰ ሊፈትሽ ነው? ምን የሚሉት አሰራር ነው? በዛ ላይ ዳር ድንበርና ህገመንግስታዊ ስርአት እንዲጠብቅ የታጠቀን መከላከያ “ውረስና ተጠቀምበት” ማለት አደገኛ ፍቃድና ስልጣን መስጠት ማለት አይደለም ወይ? መከላከያን የሚያክል ክቡርና የታጠቀ ተቋም “ነጥቀህ ተዳደር” ማለት በፍጹም መንግስታዊ አካሄድ አይደለም። መከላከያ የሚተዳደረው በበጀት ነው። እንደ ነጥቆ በረር፣ እራትህን እየሸመጠጥክ ብላ የሚባል ተቋም አይደለም። ተቋሙም ይህን አዋራጅ ተልእኮ የሚቀበል አይመስለኝም። ሃሳቡም አደገኛ ነው። በታሪክ የኢትዮጵያን ሰራዊት እንዲህ አይነት ስራ ተሰጥቶት አያውቅም። ሰራዊቱም ህዝባዊ ባህርይውን የሚፈታተኑና የሚሸረሽሩ ተልእኮዎች ሲሰጡት ሁለቴ ማሰብ አለበት። በደርግ ጊዜ የነበረው ሰራዊት እንኳን በውጊያ በፈረሰበት ጊዜ፣ ጠበንጃውንም ይዞ ቢሆን አስፈራርቶ ለመብላትና ለመጠጣት አልሞከረም። የያዘውንም ጠበንጃ ለመሸጥ አላሰበም። ይልቁንም ባለፈበት መንደርና ቤት ሁሉ የሚበላና የሚጠጣ እንዲሰጡት በልመና ይጠይቅ ነበር እንጂ። የዚህ ዓይነት ስራ እንኳንና ለመከላከያ፣ ለፖሊስም የሚመች አይደለም። ብዙ ህግና መመሪያ ወጥቶለት ይደረግ እንደሆነ እንጂ ዝም ብሎ ያገኘኸውን ውሰድ አይባልም።

ይህ ነገር ለፖሊሶችም የተሰጠ ስልጣን እንደሆነ ጠሚሩ ተናግረዋል። ይኽ ማለት የክልል ፖሊሶችና ምልሻዎችና ልዩ ኃይሎች ይሳተፋሉ ማለትም ነው። ምን አይነት የተመሰቃቀለና የተረባበሸ ህውከት እንደሚፈጠር አስቡት። የሚፈጠረው ስጋት ይታያቹህ? በዚህ ስጋት ውስጥ ያሉት ሰዎች ገንዘባቸውን ወደ ንብረት ለመቀየር ሲሉ የሚፈጠረው የዋጋ ንረት ወይም ኢንፍሌሽን ገበያውን እንዴት እንደሚያዛባው ይታያቹህ? ወደ ጎረቤት አገር የሚሸሽ ገንዘብ ብዙ ነው። እንደገናም በጥቁር ገበያ ወደ ውጭ ምንዛሬ የሚሄድ ገንዘብም ብዙ እንዲሆን ያደርገዋል። የኢትዮጵያ ባንኮች እርስ በራሳቸው ገንዘብ የሚቀባበሉት እሰካሁን በአካል ጥሬ ገንዘብ እየቆጠሩ ነው። አንድ የምናውቀው ሰው ከንግድ ባንክ ወደ አቢሲንያ 20 ሚልዮን ብር ማስተላለፍ ፈልጎ 20ውን ሚልዮን በጆንያዎች ተደርጎ በአጃቢዎች እንዲሸኝ መደረጉን፣ እዛም ሄዶ ብሩ ሲቆጠር ብቻ 5 ሰአታት እንደፈጀ ነግሮኛል። ውረሱ የሚባል ነገር ለውጭ ምንዛሬ ካልሆነ፣ የራስህን ገንዘብ ለዚህ አይነት አደጋ የሚዳርግ ከየት የመጣ አሰራር ነው? ይኽ የግድ ነው እንኳን ከተባለም፣ በግልጽ አሰራር፣ በአዋጅና በህግ እንዲሁም አግባብ ባለው ተቋም እንዲፈጸም ይደረጋል እንጂ፣ ዝም ብሎ እንደ ቀላል ነገር በደመ ነፍስ የሚወሰኑ ነገሮች ኢኮኖሚውን በጣም ነው የሚጎዱት።

እንዲህ ዓይነት የገንዘብ ለውጦች በትክክለኛው ዝግጅትና ለትክክለኛው ዓላማ ሲደረጉ የተወሰኑ ችግሮችን ይፈታሉ። እንኳን እንደዚህ በተዘረከረከ መንገድ ቀርቶ በአንዲት መጠነና ስህተት እንኳ፣ ኢኮኖሚውን በአጠቃላይ፣ ህጋዊውንና ደሃውን የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ በተለይ እጅግ አሳዛኝ ለሆነ ጉዳት ይዳርጉታል። የኢትዮጵያ ህዝብ አብዛኛው ገጠር የሚኖርና በእርሻ የሚተዳደር ነው። ይኽም ማለት ከባንኮች አገልግሎት ጋር ሙሉ ለሙሉ የተሳሰረ ህይወት የለውም። ባንኮችና በየገጠሩ ያለው አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ህዝባችን የያዘውን አነስተኛ ጥሬ ገንዘብ የባንኪ ሂሳብ ከፍቶ እንዲያስቀይርና እንዲያስቀምጥ ማስገደድ፣ ከእለታዊ የገጠር ግብይቶች ሂደት እንዲስተጓጎል ማድረግ ማለት መሆኑን ልብ ይሏል። በዚሁ ላይ ይኸ ከእጅ ወዳፍ የሚኖረው ህዝባችን ወደዚህ ዓይነት አሰራር ለመግባት፣ (ለምሳሌ፣ ለመጓጓዣም የሚከፍለው ወጪ፣ የእርሻ ሥራው በመተጓጎሉም፣ banking cost) የሚከፍለው ዋጋ ተጨማሪ ጉዳት ነው።

በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ዋዜማ፣ ኤርትራ የራሷን ገንዘብ በማተሟ ምክንያት በኢትዮጵያም የብር ለውጥ ተደርጓል። አሁን ያለው ብር ያኔ የወጣ ነው። ያኔም እንዲሁ አሮጌ ብሮች ተቀይረው የሚያልቁበት የተወሰኑ ሳምንታት ጊዜ ተሰጥቷል። በሚድያ የዘገብነው አንድ አሳዛኝ ታሪክ ነበር። ሴትየዋ ልጆች አልወለዱም፣ አላገቡም፣ መሬት አላቸው 3 የሚሆኑ ከብቶቹም ነበሯቸው። ታዲያ ልጅ ለመውለድ ካላቸው ጉጉት የተነሳ ራቅ ወዳለ ቦታ ሄደው የታወቀ የአንድ ሰዋራ ደብር ጸበል ሄደው መሰንበቻቸውን ለመታጠብ ያስባሉ። በዚያ ሁኔታ ከብቶቻቸውን የሚያቆይላቸው ወዳጅ ዘመድ አጥተው ሸጠውና ወደ ብር ቀይረው ለመሄድ ወሰኑ። ሰነባብተው ሲመጡ ብር ቅየራ ታውጆ፣ የመቀየሪያ ጊዜውም አልፎ ደረሱ። ከዚያማ ጥርስና ጥርስ ማፋጨት ሆነ።

ስለዚህ፣ መንግስት ለራሱ ምቾትና በራሱ ስሌት የሚወስናቸው ውሳኔዎች የድሃውን ዜጋ ተስፋና ኑሮ ደፍጥጦት ያልፋል። ዘንድሮም የዚህ ብር ቅየራ ሰለባዎች ብዙ እንደሚሆኑ ይታመናል።

~//~

305 COMMENTS

  1. obviously like your web site however you have to check the spelling on quite a few of your posts. Several of them are rife with spelling issues and I in finding it very bothersome to inform the truth on the other hand I will surely come again again.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here