ምርጫ 2012 በትግራይ የመጀመሪያው የተወዳዳሪ ፓርቲዎች የክርክር መድረክ

195
902

በትላንትናው የትግራይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የመጀመሪያው የክርክር መድረክ፣ “አሸናፊ” “ተሸናፊ” የሚል ብይን አልሰጠውም። ሌላ ግልጽ አሸናፊ ግን ነበረ። አሁን ትግራይ የጀመረችው የምርጫ ሂደት፣ ዋናው መለያ ባህሪያቱ ምንድናቸው ከሚለው ብንነሳ፣ ጥቂት ቁልፍ ቁምነገሮች እንጠቅሳለን። አንዱ፡ የትግራይን የራስ እድል በራስ የመወሰን ሉአላዊ መብትና ስልጣን መገለጫ ነው። ሁለት፡ አሁን ከሚታየው የፈደራል መንግስት የመብት ነጠቃና የስልጣን ጠቅላይነት የመከላከል (“መኸተ” ይሉታል ትግራዮች) አቋም ነው። ሶስት፡ የትግራይን ክልላዊ ብሄራዊ መንግስትነት በህጋዊ መንገድ የማስቀጠል ተልእኮ ነው። አራት፡ የተሻሉ አሸናፊ ሃሳቦች፣ ድርጅት/ድርጅቶችና የህዝብ ተወካዮች የማስገኛ መድረክ ነው። አምስት፡ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ራሳቸውና የድርጅት አቋሞቻቸው አስተዋውቀውና ተፎካክረው በሚያሳዩት ብልጫ የህዝብን ልብና ይሁንታ በመግዛት ስልጣን የሚወስዱበት የውድድር መድረክ ነው። ስድስት፡ ትግራይ፣ የኢትዮጵያን ህገመንግስትና ህብረብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርአት አደጋ ላይ በወደቀበት በአሁኑ ሰአት ይህንን የጋራ አገራዊ ተስፋና ህልውና ለማስቀጠል የሚኖረው ዕድል ጥርስን ነክሶ መታገልና ሉአላዊ ስልጣንን አሳልፎ ባለመስጠት መሆኑን በጽናትና በተግባር በማሳየት እንደገና ለሌሎች የኢትዮጵያ ብሄር-ብሄረሰብ ህዝቦች ተምሳሌት የምትሆንበት ሂደት ነው። ከዚህ አኳያ ከ1 እስከ 4 ባሉት ቁልፍ መመዘናዎች አሸናፊ የሚያደርጉት ተወዳዳሪዎቹን ሳይሆን ትግራይንና የትግራይ ህዝብን ነው። ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ብልጫ ይዞው በመገኘት ለደረጃ የሚወዳደሩባት አምስተኛዋ ብቻ ናት። ስደስተኛ፣ ሊሎች ኢትዮጵያውያንን የምትመለከት ናት። ስለዚህ ሂደቱ በዚህ መልክ በመጀመሩ በጎላ መልኩ አሸንፈው የወጣው የትግራይ ህዝብ ናቸው።

5 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመጀመሪያ ዙር ክርክራቸውን በተሳካ ሁኔታ አከናውነዋል። የተከራከሩበት አጀንዳ “ዲሞክራሲ፣ የራስን ዕድል በራስ ስለመወሰን መብትና የነገዋ ትግራይ” በሚሉ ሶስት ጥቅል ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበረ። ፖሊሶዎቻቸውና አፈጻጸማቸው በተመለከተ መጪዎቹን ክርክሮች አይተንና ሙሉ ስእል ይዘን ብንገመግማቸው ይሻላል። ልጅ ሲወለድ ውልደቱ ላይ ያተኮረ ደስታ ነው የሚጎላው። ከዚያ ባለፈ ምናልባት የስሙ አወጣጥ ላይ፣ ለህጻኑ ስለሚደረገው እንክብካቤ ላይ የሚደረጉ ውይይቶች ይኖራሉ እንጂ ኢንጅነር ይሁን ኳስ ተጨዋች የሚለው በይደር የሚያዝ አጀንዳ ነው። አሁን በዚህ ማስታወሻ ማሳየት የፈለግኩት ሃሳቦችን ሳይሆን ድባቡንና አቀራረቡን የሚመለከት ነው። በዚህ መንፈስ፣ ውይይቱ የተደራጀበት ሁኔታ፣ የተወዳዳሪዎቹ ዝግጁነት እና መድረኩ በምርጫው አጠቃላይ ሁኔታ ላይ የሚኖረው ፋይዳ አስመልክቼ በመጠኑ ላስቃኛቹህ።

ከጥቃቅን መሰል ጉዳዮች ልነሳ። ፓርቲዎች የሚለዩበት አንዱ ምልክት አርማቸው ነው። በምርጫና ድምጽ መስጠት ወቅት፣ ሌላው ወሳኝ መለያ ደግሞ የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት ነው። ወደፊት ተከራካሪዎች መድረክ ሲይዙና የሚውክሉትን ድርጅት አቋም ሲያስተዋውቁ ከጎናቸው ባለው ስክሪን አርማውና የመወዳደሪያ ምልክት መለጠፍ ያለበት ይመስለኛል። መራጩም፣ ከሚናገሩት ቁምነገር ጋር እያዛመደ እንዲያስታውሳቸው ይረዳል። በተለይም አሁን በነበረው መድረክ ላይ፣ ከኋላቸው የድርጅቶች አርማዎች ተሰቅለው ስለነበረ፣ በሚያወሩበት ጊዜ የካሜራው አቅጣጫና አቀማመጥ በፈጠረው ሁኔታ ከማይመለከታቸው አርማ ጋር አያይዟቸው ስክሪኑ ላይ ለረዥም ጊዜ ይቆይ ስለነበረ፣ ልክ አይሆንም። ሌላው ችግር የማይክሮፎን መቀባበልና መዋዋስ ነው። ይኽም በጣም ሊታረም የሚገባ ከባድ ያልሆነ ግን አሸማቃቂ ሁኔታ ነው። በተጨማሪም፣ አንድ ፓርቲ ወክለው የመጡ ሰዎች- ለኮቪድ የሚደረገው ጥንቃቄ እንዳለ ሆኖ- ለመመካከር ወይም ማስታወሻ ለመቀባበል በሚያስችላቸው ሁኔታ ተቀራርበው መቀመጥ ይኖርባቸዋል።

ዓረና ለዲሞክራሲና ሉአላዊነት በኢህአዴግ ዘመን በትግራይ ማህበራዊ መሰረት ይዞ የተቋቋመ የመጀመሪያው ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅት ነው። የአቢይ አህመድ ለውጥ ተከትሎ በትግራይ ህዝብ ላይ አስቀያሚ ጥቃቶች በበረቱበት ማግስት ጽኑ አቋም ይዞ ለመከላከል የሞከረ አመራር የነበረው ድርጅት ነበር። ኋላ ላይ ያጋጠሙ ችግሮች ጠለቅ ብየ ባላውቅም አሁን ባለው የትግራይ የፖለቲካና የምርጫ ታሪካዊ ሂደት ላይ እንዲሳተፍ የምፈልገው ድርጅት ነበር። በትላንትናውም መድረክ ቀርቦ ቢሆን የዓዴፓን አቋም ለማጠናከር አጋዥ ሚና ይኖረው ነበር ብየ አስባለሁ። ዓረና ከአረጋዊ በርሀ ወይም ከብልጽግና ጋር የሚያስተሳስረው ባህርይ ያለ አይመስለኝም። ለምን እንዳልተመዘገበና እንዳልተወዳደረ እምብዛም አጥጋቢ ምክንያት አይታየኝም። አንዳንዴ የአንድ ትልቅ ማህበረሰባዊ ሂደት ተሳታፊ በመሆን ያለው ትሩፋትና ከሂደቱ ለምቅረት ወይ ለመውጣት ሲወሰን መነሻ የሚሆነው ምክንያት ሲተያዩ የትየሌለ ናቸው። በዚህ ቅሬታ ወደ ክርክሩ ልመለስ።   

የመድረኩ አደረጃጀት፣ የመጀመሪያ መከራከሪያ አጀንዳ አመራረጥ፣ የጊዜ ድልድሉ፣ የክርክሩ ቅደም ተከተል መልካም የሚባል ነው። በዚህ አጭር ጊዜ በዚህ መልኩ መቅረብ መቻሉ የሚመሰገን ነው። ከዚህ አንጻር፣ የሚነቀፍ መሰረታዊ ህጸጽ አልታየበትም። የአወያየቹ ብቃትና ሚዛናዊ አያያዝ ጉልህ ነበር። የተወዳዳሪ ፓርቲዎች- ሁሉም ለማለት ይቻላል- ሃሳቦቻቸውንና አቋሞቻቸውን በልበ ሙሉነት ለማስረዳት ሳይቆጠቡ ግን ደግሞ ለዘብ ያለና ኳኳታ ያልበዛበት ጭምት አቀራረብ ነበር የተከተሉት። ይኽንንም ያደረጉት የትግራይን ህዝብ ለማክበርና እሱን ለመምሰል የመረጡት አቅጣጫ ይመስላል። በጣም ጠቃሚ ውሳኔ ነበር።

አንድ ጉዳይ ለማንሳት፣ በቁም ነገር ደረጃ፣ ሌላውን ጠቅሞ ትግራይን ብቻ ሊጎዳ የሚችል የስርአት ለውጥ ይኖራል ተብሎ አይገመትም። አሁን ያለው ስርአት ሲመጣ ግን የትግራይ ጀንበር እንደጠለቀች፣ የሌሎች ኢትዮጵያውያን አዲስ ፀሃይ እንደወጣች ተደርጎ ሲስተጋባ የነበረው ትርክትና ጫጫታ ለጉድ ነበር። ስድቡም ስሜቱም ሌላ ነበር። በእንደዚህ አይነት ጊዜ እንደ ትግራይ ህዝብ የተበዳይነትና የተካጅነት ስሜት ይዞት ብዙ ገንቢ ያልሆኑ ግብረ-መልሶች ውስጥ ሊገባ ይችል ነበር። ህዝቡ ግን ቀጥ ብሎና መሬት ይዞ፣ በዝግታና በጭምትነት፣ በአቧራው ጨሰ ሳይደናበር፣ ከሃዲድ ሳይወጣ፣ የማይታለፍ የመብት ጉዳይ ሲገጥመውም እየተጋፈጠ ነበር የዘለቀው። ዛሬ በዚሁ መድረክ የቀረቡት እጩ ተወዳዳሪዎቹም ክፉ ቀኑን አብረውት የተጋፈጡ የራሱ ልጆች ናቸው። በዚሁ የክርክር መድረክ ጎልቶ የታየው ከስሜት የራቀ፣ ጨዋና ጭብጦች ላይ ያተኮረ ክርክር፣ ከላይ ያነሳሁትን ከህዝቡ ማህበራዊ ፋይዳና እሴት የመነጨ፣ እና እሱኑኑ ያንጻባረቀ መንፈስ ነው።   

የቀረበው ይዘት ላይ ትችት ማቅረብ አልፈልግም። አወያዮቹ የተሰጣቸው ኃላፊነት መድረኩን ማስተናበር እንጂ እየቀረቡ የነበሩትን ይዘቶች መሞጎት ስላልሆነ የተባሉትን አቋሞችን ወደ ሚዛን የሚመልስ ጣልቃ ገብነት ማድረግ አይችሉም ነበር። የመድረኩም ፎርማት፣ የፈለጉትን ተናግረው ለመሄድ የተመቸ ነበር። እንደዛም ሆኖ የተከራካሪዎቹ ጠንካራ ጎን እና ክፍተት ለመገንዘብ የቻለ ሰው ይኖራል። የቀረቡትን አቋሞች በቀጥታ ከመደገፍና ከመንቀፍ ይልቅ በትላንትናው ዕለት ከተነሳው የክርክር ርእስ ጋር ተነስተው ቢሆን ብየ ያልኳቸውን ወይም ወደፊት ፓርቲዎቹ ቢያዩዋቸው ያልኳቸውን ነጥቦች አንስቼ ላገባድድ።

የትላንትናው አጀንዳ አሁን ያለንበትን መድረክ በደንብ መፈተሽ የቻለ አልነበረም። ዴሞክራሲም፣ የራስ እድል በራስ የመወሰን መብትና ስልጣንም ሲተነተኑ፣ አሁን ትግራይና ኢትዮጵያ ከሚገኙበት አሳሳቢ መድረክ አንጻር ሳይሆን በመደበኛ የአዘቦት ፖለቲካዊ ሁኔታ እንዳለን ተደርጎ ነበር የታየው። ለምሳሌ የትግራይ መጪ ሁኔታ የሚለው ጭራሽ የህልውና አደጋው እንደታለፈ ታስቦ ወይ እንደሌለ ሆኖ ነው የተወሰደው። ነገር ግን የክርክሩ ገዢ ሁኔታ በተለይም መጪዎቹ 5 አመታት “የመኸተ” አመታት እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም። የሚመረጠው መንግስትም ከመደበኛ የመንግስት ስራ በተጨማሪ ከዚህ ልዩ ሁኔታ ጋር የሚያያዙ ተግዳሮቶች ይጠብቁታል። ለዚህ የትግል መድረክ የተሻለው ፓርቲ የትኛው ነው የሚል የፓርቲዎቹ ሃሳብና አቋም ሊፈተሽበት የሚገባ ነጥብ ነበረ እላሎሁ።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ሌላው ጥርት ያለ አቋምና እይታ ያልጎበኘው ትግራይን ከኢትዮጵያ አንጻር ስላለው አያያዝ እንዴት መሆን አለበት የሚለው ነው። ይህ በመጪዎቹ ወራት የትግራይን እድልና ቀልብ ወጥሮ የሚይዝ ትልቁ አጀንዳ እንደሚሆን ይታወቃል። ማንኛውም ተወዳዳሪ ፓርቲ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚኖረው አቋም ማወቅ አስፈላጊ የሚሆንበት ሁኔታ ግልጽ ሆኖ ይታያል። ለምሳሌ ከመስከረም በኋላ በአገር ደረጃ ስላለው ሁኔታና በትግራይ ላይ የሚኖረው እንድምታ ምንድነው? የትግራይ መንግስት ከፈደራል ተቋሞች ጋር የሚኖረው ግኑኝነት በተመለከተ ፓርቲዎቹ ምን ያስባሉ፣ የትግራይ ምርጫ ውጤት በኢትዮጵያውያን እና በሌሎች የአካባቢው ኃይሎች ተቀባይነት እንዲኖረው ስለማድረግ ያላቸው አመለካከትና አማራጭ ምን ይመስላል? በዚህ ውስጥ እንደ አንድ ቢሆንታ (scenario) ከፈደራል መንግስት ጋር ወይም ክሌላ ክልል መንግስት ጋር ወይም ፓርቲ ጋር ወደ ግጭት ቢኬድ ወይም እንዳይኬድ ለማድረግ፣ የሚታሰቡ መላምቶችና መፍትሄዎች ምንድናቸው? ወዘተ…

የሁሉም ፓርቲዎች የአስተሳሰብ ምሰሶ የተተከለው ትግራይ ላይ ነው። መነጽራቸው የትግራይን ጥቅምና መብት ከማስከበር አንጻር ነው። ይኽ እስከአሁን የጠፋው አዲስ አበባን ማእከል አድርጎ የማሰብ ንጽረት በህፀፅነት የፈረጀ ይመስላል። ይሁንና ሚዛኑ ልክ የሚሆነው ምን ያህል ሲሆን ነው የሚለው ነው። በደንብ ጠበቃ ያልነበረው አቋም፣ ኢትዮጵያን እንደ አገራዊ ማንነትና ልኡል ፋይዳ ያለው ትእምርት የመገንዘቡ ነገር ነው። ከ5ቱ አራቱ ፓርቲዎች ትግራይ በኢትዮጵያ አገራዊ ጥላ ስር ያለችና የምትቀጥል ብሄር ስለመሆኗ አሁን ያነሱት ጥያቄ የለም። ከነዛ ውስጥ አንዱ ተማካይነቱን ወደ ኮንፌዴሬሽን ይበልጥኑ ማላላት ያስፈልጋል፣ ብሏል። የትግራይ ሙሉ ነጻነት መቀዳጀት ያስፈልጋል የሚለውም ድርጅት ቢሆን በሰላማዊ መንገድና በህጉ መሰረት እንዲሆን እታገላለሁ፣ ነው የሚለው። ስለዚህ ይህ ሂደት ተጀምሮ ወደ ውጤት እስኪደርስ ድረስ አሁን ትግራይ ከኢትዮጵያ ጋር ናት። ሌሎቹ ተፎካካሪ የትግራይ ፓርቲዎች፣ ኢትዮጵያን ያዩዋት እንደ አስፈላጊ ገበያ ወይም የጥቅም ማህበር እንጂ በመስዋእትነትም ጭምር መቀጠል እንዳለበት አገራዊ ማንነት አይደለም። ይኽ ከተለመደው የትግራዮች ኢትዮጵያን የሚያዩበት መነጽርና አተያይ ትንሽ ፈቅ ያለ መስሎ ተስምቶኛል። ትግራዮች ለኢትዮጵያ ያላቸው ስሜት በዘመናት መካከል እየተቀየረ ይሆን? የሚል ጥያቄም አጭሮብኛል።

በኢትዮጵያዊነት ጽንሰ ሃሳብ ቋሚ ጉዳት እየደረሰ ሰለመሆኑ አንዱ ማስረጃው ይኸው የትላንትናው መድረክ ነው። የጨለማ ዘመን እያሉ፣ ገራፊውን ትግርኛ ተናጋሪ እያሉ፣ 5% ለ95% እያሉ፣ ኦሮማራ እያሉ፣ እንዲሁም ዛላንበሳንና ሰርሃን በግንብ አጥረው ሲያበቁ አዲስ አበባንና አስመራን እያገናኙ፣ የፈጠሩት ስሜት ነው። እንጂማ ትግራይ ኢትዮጵያን በደሙና በአጥንቱ ሲከላከልላት እንጂ በሰጥቶ-መቀበል ስሌት አዋጭነቷ አይቶ የሚያቅፋትና የሚገፈትራት ፕሮጀክት አልነበረችም። የህወሓት ሰዎች እንኳን ለመጀመሪያ ጊዜ በረሃ እንደወጡ የነበራቸው የትግራይ ሪፓብሊክ ፕሮግራም ያስተካከለላቸው የትግራይ ገበሬ ነበር። የመጀመሪያው ወያኔ ሲነሳ፣ “የምንተዳደረው በወዛችን፣ የምንዳኘው በወንዛችን፣ ባንዲራችን የኢትዮጵያ” የሚል  አዋጅ ነበረው። አጼ ኃ/ስላሴ የእንግሊዝ ጀቶች ከየመን ድረስ አስመጥተው የመቀሌ ገበያ ሲደበደቡም ይኽ አቋም አልተቀየረም ። ደርግ ሓውዜንን ሲደበድብ፣ ይኽ ስሜት በቦታው ነበር። ከ10 አመት በፊት ሞተር ሳይክል ተፈናጥጬ (የመኪና መንገድ የለውም) አንድ እልም ያለ ገጠር ውስጥ የዘመድ ስርግ ለመገኘት ሂጄ ነበር። በዚያ ከከተማና ከመኪና መንገድ ርቆ ያለ ቦታ ስንደርስ ግን ዳሱ በልምጡ ባንዲራ ደምቆ፣ የአማርኛ ሲዲ በጂኔሬተር ኃይል ሲዘፈን ደረስኩ። እንደኔ እንግዳ ሆኖ የተገኘ ካልሆነ እዚያ ቦታ አንዲት የአማርኛ ቃል የሚያውቅ ሰው መኖሩን እንኳ እጠራጠራለሁ። እንግዲያማ እንዲያ የሆነው ለዘመናት በተሻገረው ትሥሥር ነው እንጂ የዲፕሎማሲ ታይታ ወይ ገበያ ጥቅም እያሰበ ያደረገው አልነበረም። የአማራ ልሂቃንና ሚድያዎች በማወቅም ባለማወቅም በአዲሱ ትውልድ ዘንድ እየፈጠሩት የመጡት የጥላቻ ስሜት ይኸው ከቡቃያ ወደ እሸት አድርሰውታል።

በትላንትናው ዕለት በነበረው የትግራይ ፓርቲዎች ክርክር ፓርቲዎቹ ዘንድ ጎልቶ የወጣ አሸናፊም ተሸናፊም አልነበረም ብያቹሃለሁ። ነገር ግን በግልጽ አሸናፊዋ ትግራይ ነበረች።  በጣም አጉል የፖለቲካ መፋለሶችን ሁኔታዎችን ፈጥሮ ኢትዮጵያን ማረጋጋት ያቃተውና ምርጫ አታድርጉ ሲል ትግራይን ያስጠነቀቀው የብልጽግና አመራር ክርክሩ ላይ አልተነሳም፣ አልተወሳም። ይኽም አስገራሚ ነበር። በመድረኩ ስለ ኢትዮጵያም፣ ስለ ፈደራል መንግስትም የተጠቀሰበት ምሽት አልነበረም።

የምርጫ ኮሚሽኑ በዚህ ፍጥነት መንቀሳቀሱ እና የተነቃቃ ሁኔታ መፍጠሩ የሚደነቅ ነው።

ትግራይ ምርጫ 2012

195 COMMENTS

  1. I don’t even know how I ended up here, however I assuymed this submut was great.
    I do not realize who you are however ertainly you’re going to a well-known blogger in thhe event you
    aren’t already. Cheers!
    web site

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here