ድርድር ከጭብጦ ጋር!

172
3839

ክፍል ፫ : የመጨረሻ ክፍል

በክፍል ፩ እና በክፍል ፪ በቀረቡት ፅሑፎች ፤ እየተባባሰ ስለመጣው ችግር፤ በምናልባትነት ገቢር ሊሆኑ የሚችሉ አማራጮች (አማራጭ ከተባለ) ለመዳሰስ ሞክረናል። የመጨረሻውና በተነፃፃሪነት ሻል ያለው አማራⶽ ከትግራይ መንግስት ጋር ሊደረግ ስለሚገባው ድርድር በዝርዝር እናያለን። ይኼን አማራⶽ በእነ Iinternational Crisis Group እንደየተሻለ መወጣጫ መንገድ እየተጠቆመ ነው (የICG መነሻ የተዛባና  አቅጣⶻውም ለአንድ ወገን ያደላ ቢሆንም)። መቼስ  አንድ ሳምንት በፖለቲካ እድሜ አንድ አመት ያህል ነውና፤ የእነ ሺመልስ አዱኛ መዘክዘክ፤ የአማራ አዴፓ/ብልፅግና  እየተቆመረ ለከት የሌለው አሽርጋጅነት ፤ ማለቂያ የሌለው የካቢኔ ብወዛና ሹም ሽር፤ የአዳነች አበቤ  የአዲስ አበባ ከንቲባ ሹመት (በቁስል ላይ እንጨት ስደድበት)፤ ሰሞኑን ከተፈፀሙ ክንዋኔዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው።  እነዚህ ሁላ ከቆየው ችግር ተደምረው፤ የአገሪቷን ችግር ከማባባስና፤ የጠ/ሚር አቢይ የታወከ የመንግስት አስተዳደር ነው የሚለው ስእል ያደምቁታል፤ ፬ኛውን አማራⶽ እንድናይም ግድ ሆኗል።

ክልሎች በተለይ የትግራይ መንግስት ተገዳዳሪ አቅማቸው ተጠቅመው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ጫና በመፍጠር ወደ ድርድር እንዲመጡ ማድረግ?

በፌደራል መንግስት ላይ ጫና ማሳደር የሚችሉ አስተዳደራዊ አቅም፤ መንግስታዊ ቁመና፤ በተወሰነ መልኩም የፀጥታና የህግ አስከባሪ ሃይል ያላቸው የክልል መንግስታት ሲሆኑ እነዚህም በዋናነት ትግራይ፤ምናልባትም ኦሮምያ፤አፋር ክልል ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አሁን አሁን ድግሞ ወላየታና ሲዳማም ዳር ዳር እያሉ ነው። በተጨባጭ አብዛኞቹ ክልሎች ፌደራል መንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኙ ሲሆን የትግራይ ክልል መንግስት ግን ከጠቅላዩ ጋር ሆድና ጀርባ ሆኗል። አንዳንዶች ይህ ፍጥጫ ወደ ዘመን መሳፍንት ይመልሰን ይሆን የሚል ስጋት አላቸው፤ የመንና ሶርያም በጭንቀት ያማትራሉ። ክልሎች ልዩ ኅይል በከፍተኛ ትጥቅ ማደራጀታቸው ስጋቱን አባብሶታል። እንደ ትግራይ አይነቱ ደግሞ የኢትዮጵያ የጦር ሃይል ያደራጀና የመራ በቂ ተገዳዳሪ ሃይልና ትውልዶችና ዘመናት የተሻገረ የስኬታማ ጦርነት ልምድ ያለው መሆኑ የማያባራ ጦርነት እንዳያመጣ ስጋት መኖሩ የግድ ነው።  የዚህ ፅሑፍ አላማ፤ ይሔንን ስጋት ከግምት አስገብቶ፤ ይህ አማራጭ ከስጋቱ ይልቅ ተስፋው የተሻለ መሆኑን ማሳየት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛቻቸውን ትተው ወደ ድርድር ለማምጣት የሚያስችለው መንገድ የተሻለ አማራጭ ይሄው ነው ብሎ ይኼ ፀሃፊ ያምናል። የትግራይ መንግስት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ይኼን ተከትለው የራስ ማስተዳደር መርህ መሰረታዊ ትርጉም ከክልል እስከ ወረዳ politics is local በሚለው መርህ በባለቤትነትና በሙሉዕነት ስራ ላይ ቢያውሉት የተሻለ ውጤት በድርድር ማምጣት ይቻላል። እንዴት? ማንኛውም ሃይል እንዲደራደር ለማስገደድ ሁለት አውራ ጉዳዮች መሟላት ይኖርባቸዋል፡ቁመና (posture essentially from hard power) እና ጭብጦ (what you have to offer essentially from soft power)

ቁመና ስንል ምን ማለታችን ነው?

የመንግስት የመጀመሪያው ስልጣንና ህዝባዊ ቅቡልነትና (authority and legitimacy) የሚመንጨው፡ የጋራ ድህንነት መጠበቅና ከሞላ ጎደል የህግ ማስከበር አቅሙ ነው (collective security and law enforcement capacity)። በመንግስትና በዜጎች መካካል ያለው የመጀመሪያው መሰረታዊ ኮንትራት ይኽ ነው። ይህ የለም፤ መንግስት የለም። አንድ ሰው ከእነቤተሰቡ ከገበያም ይሁን ከስራ ገበታ ወይ ከዘመድ ጥየቃ በሰላም ውሎ መመለስ ካልቻለ የስም መንግስት ምን ትዳው? የአሁኗ ኢትዮጵያ “መንግስት የለም” “የት ያለ መንግስት” የሚባል የዕለት ተዕለት ምሬት ልክ  እንደ “እንደምን አደራቹህ” የዘወትር ሰላምታ ከሆነ ሰነባብቷል።  ለዚህ ለዚህ እንደአቅሚቲ የግል ጠባቂ ከፍ ሲል ደግሞ የሰፈር ሪፓብሊካን ጋርድ ማደራጀት ሳይሻል አይቀርም። በአንፃሩ ይህ ትግራይ ውስጥ ችግር አይደለም፤ ከፀጥታና ህግ ማስከበር አልፎ፤ ለህብረተስቡ መሰረታዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አግለግሎት ይሰጣል። አጥንቱ የደነደነ በተግባር የተፈተነ ሰፊ ማህበራዊ መሰረት ያለው የፀጥታ ሃይልም አለው። ቢያንስ ቢያንስ የራሱንና የአከባቢውን ፀጥታና ድህንነት የመጠበቅ አቅም አለው። ቁመና ማለት ይህ ነው።

ቁመና ሳይኖርህ፤ ሃይልህን ፕሮጀክት ማድርግ አትችልም፡ ተቀናቃኝህም ያአንተም የራሱም አቅሙ እንዲገምት ከፀብ ጫሪነትም ለዘብ እንዲል ቁመናህን በማዶም ቢሆን ማየት ይኖርበታል። ፌደራል መንግስቱም፤ በተሰጠው ሃላፊነት ልክ የሚመጥን የፀጥታ የማስከበር አቅም ባይኖረውም፤ ቢያንስ መቀመጫውንና አንዳንድ ከተሞችን የመቆጣጠር አቅም ይኖረዋል። በተጨማሪም ከፍተኛ ወታደራዊ ቁሳቁስና የፋይናንስ አቅም ከአይዞህ ባዮች እንደሚያገኝ (በተለይ ከግብፅና ሌሎች የአረብ መንግስታት) ጥርጥር የለውም። በአጭሩ የተወሰነ የማይናቅ ቁመና አለው። አብዛኛዎቹ ሌሎች ክልሎች ይኼን በተመለከተ በየአይነቱ ዝብርቅርቅ ነው። ከአንድ ጫፍ እየተንገዳገደ በድጋፍ ሊቆም የሚችል አለ ወደ አንዱ ጫፍ ደግሞ ፍፁም የተንበረከከ በተላላኪነት የሚመደብ ነው።  እንደ አብዛኛው የአማራ ክልል ለጎጥ ሽፍታ ያደረም አለ። ስለዚህ ፌደራሉን ከሚግደራደርና ሙሉ ቁመና ካለው የትግራይ መንግስት ላይ ትኩረት ማድረጉ ግድ ነው።

ጭብጦ

ቁመና ለጦርነት በቂ ሊሆን ይችላል፤ ለድርድር ግን ጭብጦ ግድ ነው። በቁመና ፕሮጀክሽን ተገዳዳሪነትክን ካሳይህ በኋላ የምትቀበለውን (demand) ለማግኘት የምትስጠው ጭብጦ ሊኖርህ ይገባል (offer)። የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት offer የሚያረገው ብዙ ነው፤ ስልጣን መጋራት፤ፋይናንስ፤ ገበያ፤ አለማቀፍ ድጋፍ፤ አገናኝ መድረክ (ሁሉም በግልፅ በሚያውቀው ጉዳይ ከዚህ በላይ መዘርዝሩ አስፈላጊ አይደለም)።

የትግራይ መንግስትስ ከቁመና በላይ ምን አለው? 

ክልሎች የራሳቸው፤ የአጎራባች ማናጋት የሚችል፤ አልፎም  የፌደራል መንግስት ፀጥታ የማስከበር ሃይል የሚፈታተን ለዱላም ይሁን ለድንጊያ ክምር፤ ለቦንብም ይሁን ለጥይት  የሚበቃ በወግ የታጠቀም፤ በመንጋ የሚሰማራም አቅም እንዳላቸው፤ ከአማራ እስከ ጉጂ፤ ከኦሮሚያ እስከ ወላይታ በተግባር እያየነው ነው።  የትግራይ መንግስት ግን ከራሱ አልፎ ለአከባቢው የሚበቃ የፀጥታ ዋስትና አቅም አለው (hard power)። ይኼም በተግባር የታየ ነው። ነገር ግን ትርጉም ላለው የፓለቲካ አገራዊ መፍትሔ ድርድር ግድ ነው። ሰላማዊ ድርድር ከወታደራዊ ቁመና በላይ ዳጎስ ያለ ጭብጦ ያለው ሶፍት ፖወር መያዝ ይኖርበታል። አንዱም ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ሙሉ በሙሉ የትግራይ ህግ-መንግስት በሚያዘው መሰረት ሲያከናውን ነው።  የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ከመንግስት ሃላፊነቱና ግዴታዎቹ አንዱ፤ ወቅቱን ጠብቆ በክልሉ ህገ መንግስት መሰረት ምርጫ ማካሄድ ነው። አሁን አይንህ ለአፈር እንደተባባሉት የኢህአዴግ ወዳጆቹ ፤ ህወሓትም ቢሆን በጉልበት የተገኘ ስልጣን እንጂ በምርጫ የተገኘ ህዝባዊ ቅቡልነት እስካሁን የለውም። አሁን በትግራይ ሕዝብ ጫና ወዶም ይሁን ተገዶ ምርጫ ማካሄድ ይኖርበታል። ምርጫው ተፎካካሪ ፓርቲዎች (ዓሲምባ፤ውናት፤ሳለሳይ ወያነ፤ ባይቶና፤ ወዘተ) የግል ተወዳዳሪዎች ጋር በግልፅና በእኩልነት የተሳተፉበት መሆን ይኖርበታል። ሂደቱም፤ አተገባበሩም የሚወሰነው እዛው ትግራይ ነው። ትግራይ ይኼን የማድረግ አቅም ብቻ ሳይሆን፤ ምርጫ ለማስፈፀም የሚያስችል ሁኔታ (environment) አለ። የሕዝብ የስነ አእምሮ ዝግጅትም አለ። ትግራይ ይሔንን ማድረግ ይችላል፤ መደረግም አለበት። ይህ በዋናነት የትግራይ የራስ እድል በራስ የመወሰን መብትና አቅም (autonomy) ጭብጦውን ቢይዝ ለድርድር ያለው ብቃት ለማሳየት የሚደረግ ጥረት ቢሆንም በአገር አቀፍ ደረጃ ጠቀሜታው የጎላ ነው። ለምን ቢባል፡ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የማያባራ የድርድር ሂደትና ውጤት ነው። የሚገነባውም በድርድር፤የሚኖረውም፤ የሚተነፍሰውም በድርድር ነው። ታዲያ ምን ተይዞ መደራደር አለ? እንግዲህ የማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ፡ የአስቸኳይ ጉባኤ መግለጫ እየተባለ፤ ከሁለት ዓመት በላይ ሁሉም በየፊናው ኝኝ ሲሉ ከርመዋል። እንግዲህ መግለጫ ጥርስ አይሆን! ጭብጦም አይደል! የትግራይ መንግስት ‘በወቅቱ ምርጫ እንካሄዳለን’ መግለጫም ከዛቻ አልፎ፤ መሬት ላይ ጠብ ይበል። ተዓማኒነትና ሕዝባዊ ቅቡልነት እንዲኖረው፤ ከዝግጅት እስከ ፍፃሜ ተፎካካሪ ቡድኖች በእኩል ይሳተፉበት።

የዚህ ምርጫ አንዱ ልዩ ባህሪ፤ እንደተለመደው ከላይ ተሹመው መጥተው  ሕዝብ ለይስሙላ መርጠህ አፅድቅልን ከሚባለው ፍፁም የተለየ እንዲሆን ግድ ይላል። አብዛኛው ስልጣን ከአራት ኪሎ ወደ ክልል ይውረድ ስንል (devolve)፤ እዛው ክልል አዲስ ንጉስና መሳፍንት ለመፍጠር አይደለም። አብዛኛው ኗሪ የሚፈልገው የእለት ተእለት ጉዳይ ያለው ወረዳ ጋ ነው። ስለዚህ የክልል (ስቴት) ስልጣንም ፤ ከክልል ወደ ወረዳ መተላለፍ ይኖርበታል። ከህዝብ ጋር ቀጥታና የዘወትር ግንኙነት ያለው የወረዳ አስተዳደራዊ ስልጣን ነው። ይህ እርክን ካለ ምንም እንክን በፍፁም ሙለእነት ተጠያቂነቱ በቀጥታ ለመረጠው ለወረዳው ህዝብና ለወረዳው ህዝብ ብቻ መሆን አለበት።  የህወሓት መሪዎች ስለ ምርጫ ሲያወሩ ይኼንን  ለመተግበር በአስቸኳይ መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ይኼን ለመተግበር ቢትጉ መልካም ነው፤ አሊያ አራት ኪሎ እያሉ የደረሰውና እስከአሁን ዋጋ እየተከፈለበት ያለው መዘዝ መቐለም ይከተላቸዋል።

በእንደዚህ ነፃና ህጋዊ ምርጫ፤ ሕዝባዊ ቅቡልነትና የአብዛሃ ደምፅ ይዞ የመጣ መንግስት (legal, legitimate and popular) አራት ኪሎን ዘወር በል ቢል ያምርበታል። የሞራልና የህግ የበላይነት ይይዛል። እንግዲህ ጭብጦው ይህ ነው (this is the soft power)። ለሌሎች ክልሎችም አርአያ ይሆናል፤ተስፋን ይሰንቃል። በዚህ መንገድ አራት ኪሎ ላይ ተገቢ ጫና መፍጠር ይችላል። ጠቅላዩም ማጣፍያቸው ያጥራል፤ ወደ ድርድር እንዲመጡም ይገደዳሉ። ክልሉ ምናልባት ረስተው እንደሆን የወረቀት ነብር እንዳልሆነ በግቢር ያዩታል። እንግዲህ ጥቂት ብልሆች ካለፈ ልምድና ታሪክ ወስድው ባይተነብዩም መጪውን መገመት ይችላሉ። አንዳንዱ ደግሞ በሚጨበጥ በሚዳሰስ ነገር ነው የሚያምነው። ጠቅላዩ እንዲህ አይነት ሰው ቢሆኑ ሊገርም አይገባም። በተግባር በነቂስ ወጥቶ በነፃነት ሕዝብ ምርጫ ሲያካሂድ፤ ፍላጎቱንም ሲገልጽና ፤ተወዳዳሪዎችም ውጤቱን በፀጋ ሲቀበሉ፤ ጠቅላዩ በሩቅ ከመታዘብ ምን ምርጫ ይኖራቸዋል። ይኼንን የሕዝብ ፍቃድና ፍላጎት ጥሰው፤ ወጠምሻ ሪፓብሊካን ጋርድ አዘምታሎህ ቢሉ ኪሳራውም ዕዳውም ብዙ ነው። የደለበ ክብር ዘበኛ ለነጋዳፊም አልሆነ።

ቋፍ ላይ ያሉ እንደ አፋር፤ ወላይታና ኦርሚያ፤ የክልልና የወረዳ ምርጫ ለማድረግ ድፍረት ሊኖራቸው ይገባል። ከአቤቱታና ሰዶ ማሳደድ ወጥተው፤ ህዝባቸውን ማረጋጋት፤ ፀጥታ ማስከበር፤ ቅቡልነት ማግኘት መቻል ትልቅ እምርታ ነው። ለአከባቢያቸውም ለአገሪቷም እፎይታ ነው።

ከህወሓት የተናቆሩና በተለይ በሌላ ክልል የመንግስት ስልጣን  ላይ ያሉ ወይም ተገዳዳሪ የሆኑ አካላት ይኼን መስመር ለመከተል ከህወሕት ጋር መታርቅ ግድ አይልም። የትግራይን አርአያ ተከትለው ፌደራሉን ሳይጠብቁ የየአከባቢ ምርጫ ቢያካሂዱ ወይ እንዲካሄድ ግፊት ቢያረጉ ከጠቅላዩ ጋር የሚኖራቸው ድርድር በእኩልነትና ሉዑላዊነት የተመሰረተ እንዲሆን ዕድላቸው ከፍ ያረገዋል። አለበለዚያ አሁን እንደሚታየው የአማራ ብልፅግና የራስ መብትንና ሉዑላዊነት ብኩርና ሽጦ ትርፍራፊ መልቀም ነው። የልመናና ከበታችነት የመነጨ የታዛዥነት ተልዕኮም ይቀጥላል። አያያዙን (ቁመናውን) አይቶ ጭብጦውን ቀማው ነው ነገሩ።

በእርግጥ ይኼም መንገድ እንደሌላው ለእያንዳንዱ ቡድን ትርፍና ኪሳራ አለው። የዚህ ፅሁፍ መከራከሪያ ለሕዝቡ ብቻ ሳይሆን በስልጣን ላይ ላሉት መቆየትም ለሚፍልጉት ኪሳራውና ትርፉ ተወራርዶ ደም ሳይፋሰስ የሚተርፍ እርባና አለው የሚል እሳቤ ነው። የህወሓት መሪዎች፤ ከተፎካካሪዎቻቸው ጋር ተስማምተው ነፃና ፍትሓዊ ምርጫ ቢያካሂዱ፤ አቢይ መጣ ኢሳያስ መጣ፤የትግራይ ሕዝብ ከጎናቸው ይቆማል። በተግባር እንደታየው ጥላ ከለላ ይሆናቸዋል። አይ ምርጫን እንደሸቀጥ ተጠቅመው፤ ከአቢይ ጋር እሞዳሞዳሎህ ቢሉ፤ የትግራይ ሕዝብ ላያቸው ላይ ይቆማል። ምርጫው የነሱ ነው። አሁን ከአቢይ ጋር ሆድና ጀርባ የሆኑት የህወሓት መሪዎች (ለዲሞከራሲ ትልቅ ፀጋ ነው) ይኼን ማድረግ ይችላሉ። እስካሁን ላጥፉት በደልና ላደረሱት ኪሳራ፤ መካስ ጀመሩ ማለት ነው።  ሌሎች ቋፍ ላይ ያሉ የኦሮሚያና የሌሎች ማህበረሰብ የፓለቲካ ቡድኖች  ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያላቸው ግነኙነት  (አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ ) መልክ አስይዘው፤ ትግራይ እንዲደርግ የምንግፋፋውን ከክልል እስከ ወረዳ የራስ እድል በራስ የመወሰን መንገድ ቢመርጡ ያዋጣቸዋል።  ችግሩም መፍትሔውም ያለው እዛው ነው። ወረዳን የተቆጣጠረ ፓለቲካን ተቆጣጠረ! Politics is local as Tip O’Neil would love to say!

ቁመና ብቻውን ከጀብደኝነት ወይም ውንብድና አያልፍም!

ጭብጦ ብቻውን ከወንበዴ ወይም ዘራፊ አያስጥልም!

ቁመናም ጭብጦም ከተያዘ ግን የማይቻል የለም! ጥይት ሳይተኮስ ለዛውም በድርድር!

ሰሎሞን መዝገቡ

ምርጫ 2012 የራስ እድል በራስ መወሰን እና ድርድር መወጣጫውስ? ክፍል ፩

 የኢትዮጵያ የፀጥታ ቀውስና የፖለቲካ ፍጥጫ! መወጣጫውስ? ድርድር? ክፍል ፪

172 COMMENTS

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here