ለአማራው ልሂቅ፣ ወልቃይት ብቻ ሳይሆን ዛላንበሳም ያንተ ነው!

116
4754

የአማራ ክልል ወንድሞቻችን ወልቃይትና ራያ ይመለሱልን የሚለውን ጥያቄ ገፍተውበታል። ጥቂት ሰዎች ተጠራርተው ያነሱት ጥያቄ ሚድያዎቹና ልሂቃኑም ተቀላቀሉት። አሁን ደግሞ ጭራሽ አመራሮቹም ተጨምረውበታል። እንዲህ እየሰፋ መምጣቱ ብቻ ሳይሆን ጥያቄው አግባብ ባለው መንገድና ህጉን ተከትሎ ለሚመለከታቸው ተቋማትና አካላት እየቀረበ አለመሆኑ ነው። የክልሎቹ አመራሮች መጠየቅ የሚችሉት የወሰን ጥያቄ ካላቸው ብቻ ነው። የማንነት ጥያቄ ከሆነ ግን ጥያቄውን ማቅረብ የሚችለው ነዋሪው/ህዝቡ ብቻ ነው። ስለዚህ በራያና ወልቃይት የሚቀርብ የማንነት ጥያቄ ካለ ሊገርም አይችልም። ጥያቄው ባይኖር አይቀርብም። ከቀረበ ግን በባለቤቱ ስለሚሆን የሚገርም ነገር አይኖረውም። ዋናው ነገር አቅራቢው ባለቤቱ መሆኑ ላይ ነው። አቀራረቡም ህጋዊ መሆን አለበት። አሁን ያለን ህግ የዚህን ዓይነት ጥያቄ ፍትሃዊና አሳማኝ በሆነ መልኩ ለማስተናገድ አቅም ያንሰው እንደሆነም ህጉን ነው መቀየር ወይም ማሻሻል። ያም ቢሆን በህጋዊ መንገድ መሆን አለበት። ስለዚህ በየመድረኩና በየስብሰባው እንዲሁም በየሚዲያው የሚያነታርክ ነገር የለውም ማለት ነው። አሁን ከተባለው ውጭ በግጭትስ ሊፈታ ይችላል? በፍጹም። በግጭት የመፈታት ዕድሉ ዜሮ ነው። ይህን ጥያቄ የሚይዙትና የሚያጦዙት የተባሉት አካባቢዎች ሰዎች ካልሆኑ፣ ወይም የዚያ አከባቢ ነዋሪ ውክልና ያገኙ ካልሆኑ፣ አላማቸው ከጉዳዩ ውጭ ነው ማለት ነው። ይኸኛው የማንነት ስለሚባለው ነው።

የመሬትና የወሰንስ ከሆነ? አሁን ያለው የፌዴራላዊ ኢትዮጵያ የውስጥ ግዛቶችና ክልሎች አከላል ህገመንግስቱ መሰረት ያደረገ ነው። አደረጃጀቱም ብሄርዊና ብሄረሰባዊ ማንነት መሰረት ያደረገ ሆኖ ቋንቋ፣ ባህል፣ ጂኦግራፊ፣ ታሪክና ፈቃደኝነት ከግምት ያስገባ ነው። ወልቃይት አከባቢ የወሰን እና ይዞታ ችግር ጭቅጭቅ አለ በሚል በሁለቱ የክልል አመራሮችና ገዢ ፓርቲዎች ውይይቶችና ምክክሮች ይደረጉ እንደነበር ይታወቃል። በዚያ ምክንያት ግጨው አከባቢ የተመለከቱ በመግባባት የተደረጉ መሸጋሸጎችንም እናስታስውሳለን። ይሁንና ጥያቄዎቹ እየሰፉ፣ በራያ አካባቢ ያለውንም ጨምሮ እየበዙ ነው የመጡት። ከዚህ በፊት የወሰንና ይዞታ ጥያቄዎቹ የሚነሱት ከአማራ በኩል የነበሩ ቢሆንም አሁን አሁን ከትግራይም በኩል በሁለቱ አቅጣጫዎች የሚገቡን የትግራይ መሬቶች አሉ የሚሉ ጥያቄዎች በፖለቲካ ፓርቲዎች ሳይቀር መነሳት ጀምረዋል። ይኸም ግን መንገድ አለው። ሲሆን ሲሆን መሬቱም የህዝቡ ነው ህዝቡም የመሬቱ ነው። የትም አይሄድም። ስለዚህ ብዙ አንገብጋቢ የልማትና የድህነት ጥያቄዎች እያሉ ወደዚህ ማተኮሩ ፍጹም ብልህነት የጎደለው ነው። ይሁንና የግድ ይታይ ከተባለም፣ አንዱ ወይም ሁለቱ ክልሎች ይህንን ጥያቄ አንስተው መወያየትና 3ተኛ አካል ሳያስገቡ መልክ ማስያዝ ይችላሉ። ካልሆነም ህጉን ተከትለው የፌዴሬሽን ም/ቤትን ጨምረው ሊፈቱት ይችላሉ። በዚህ ምክንያት እንኳን ግጭት ጭቅጭቅም አስፈላጊ አይደለም።

ፈረንጆች speaking from the heart የሚሉት አገላለጽ አላቸው። ከይሉኝታም ከድብቅ አላማም የጸዳ ትክክለኛ ስሜትን መግለጽ እንደማለት ነው። ትክክለኛ ስሜት መግለጽ ከንግግርም አልፎ በተግባርም ሊገለጽ ይችላል። እኔ አሁን ይህችን ማስታወሻ የማጋራው በዚሁ መንፈስ ነው። ኢትዮጵያውያን በአንዲት ማሳና በአንዲት ዛፍ እርስ በራሳቸው ይጣላሉ። በዚህ ምክንያት የልማት ስራና አቅም ግንባታ ትተው ጭቅጭቅ ውስጥ ተጠምደው የመከላከል ወይም የመነጣጠቅ አቅም ይገነባሉ። ያ ሲሆን ያላቸውን ሁሉ ራሳቸውንም ጭምር ያስወስዳሉ። ራሳችንን ወደ ስልጣኔ ያስገባን ጊዜ ሁሉም የኛ ይሆናል። ከስልጣኔ ማእቀፍ ወጥተን የማይረቡ ጭቅጭቆች ላይ የተጠመድን ከሆነ ግን እያነስን እያነስን ሄደን እንጠፋለን። የአክሱም ስልጣኔ ባለቤቶች የነበርን ጊዜ ብዙ መሬትና ብዙ ባህር አስፋፍተን ስናበቃ የአለም ስልጣኔና ጉልህ ኃይል ሆነን፣ ከኃያላኑ እኩል ተቆጥረን እና ተክብረን የሚገባን ማዕረገ-ቦታ ይዘን ነበር። ከዛ በኋላ ብልጭታዎች ካልሆኑ የተረጋጋ የስልጣኔ ዘመን አልነበረንም። ግዛታችንም እየተጨረማመተ፣ እያነሰ፣ እያነሰ መጥቶ ከአክሱም በኋላ እስከ አሁን ከነበረን እያጣን እንጂ እየጨመርን አላየንም። ሶማሊላንድን ለእንግሊዝ ጂቡትይን ለፈረንሳይ የሰጠነው በቅርቡ ነው። መጨረሻ የነበረንን የባህር በር ያጣነው አሁን ትላንትና ነው። ፖለቲካችን ዳፍንታም ሆኗል። እንደ አገር የዛገ እይታ ውስጥ ገብተናል። እንግሊዝኛው state dereliction ይሏል።

እንግዲህ ፍልስፍና የተማሩ ልሂቃን ናቸው “ወልቃይት የኛው ትውልድ አድዋ ነው” የሚሉን። ይኽን የሚነግረን ምሁር ጣልያን አይደለም። ይኽንን ተናግሮም አላፈረም፣ አልተደበቀም። እንደ አዋቂ ሰው በየሚድያውና በትላልቅ መድረኮች እየተጋበዘ ይናገራል። የሚጸየፈው ሰው አለመብዛቱም እጅጉን ያስደነግጣል። ወልቃይትና ራያ የኛ ነው እያሉ በየአደባባዩ የሚናገሩ የአማራ ልሂቃን ከዚህ በጣም ጎጂ አካሄድ መቆጠብ አለባቸው። በትግርኛ “እነይ ጓሊ ዶ ዕንቁ ይሳረቓ” የሚል አባባል አለ። ሃሳቡም እናትና ልጂ ጌጥ ይሰራረቃሉ ወይ የሚል ነው። አሁን ስራ ላይ ያለው የክልሎች ድንበር የተወሰነው በቻርተሩ ዘመን ነው። ያ አከላለል ትግራይን ጠቅሟል የሚል እምነት የለም። ይህንንም በደንብ በማስረጃ ማሳየት ይቻላል። ትግራይ በቆዳ ስፋትም፣ በኢኮኖሚም በደርግ ጊዜ ከነበራት ይዞታ ጋር ሲነጻጸር ካገኘችው ያጣችው ይበዛል። ትግራይ ለምሳሌ ¼ኛ የመሬት ቆዳ ስፋቷን ቀንሳለች። የተወሰደባት ደግሞ ከፍተኛ ማለትም በመቶዎች ቢልዮኖች ዶላር የሚገመት ስትራተጂክ ጠቀሜታ ያላቸው የማእድናት ክምችት ያለበት ይዞታ ነው። አንድ አገር እስከሆንና የተፈናቀለ ሰው እስከሌለ ድረስ ይኸ ጥያቄ ትግራዮችን አላስጨነቀም።

የአማራ አመራርና ሊሂቃን ራያና ወልቃይት ማንነት የአማራ ነው ይላሉ። የአማራ ሊሂቃን ወንድሞቻችን በአዲስ አበባ ባለርሰትነትም ከኦሮሞ ወንድሞቻችን ጋር ያልተቋጨ ንትርክ ውስጥ ገብተዋል። አዲስ አበባ በኦሮሞ ምድር ፊንፊኔ ላይ ስለተቆረቆረች “የኦሮሞ ናት” የሚለውን ክርክር “የለም ፊንፊኔ ከመሆኗ በፊት ከ500 አመታት ቀደም ብሎ በረራ ትባል ነበር” የሚል ምጉት ያቀርባሉ። የሁለቱም የይገባናል ጥያቄ ነዋሪዎችን የረሳ በመሆኑ እጅጉን መስመር የሳተ ነው። የአማራ ወንድሞቻችን አቋም ግን እጅግ ሲበዛ ፈጣጣ ነው። በዚህ መልክ ይህንን ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ የሚታሰበው እንዴት ነው? አሁን ኢትዮጵያውያን መጨቃጨቅ የነበረባቸው ድህነትን ለማራገፍና ስልጣኔ ለማብሰር “በየትኛው መንገድ እንጓዝ?”  የሚል መሆን ሲገባው የትም ያልሄዱብንን የበሬ ግምባር ስለሚያካክሉት ቦታዎች እንጣላለን። የጸቡ መነሻ እየሆነ ያለው ደግሞ ጋሃዱ እውነታ ሳይሆን ታሪክ ነው። ገሃዱ እውነታ መሬቱ ላይ ያሉት ሰዎችና ህጉ ነው። ጥያቄውን ስሜቶች መኮርኮርያ ማድረግ ሳይሆን ጥያቄውን አደራጅቶ ለህጉ መስጠት ነው። መሪቱ ላይ ያሉ ሰዎችም ማንነታቸው ለመግለጽ የሚያንሱ አይደሉም። ከዚህ ሁሉ ተፈልጋ እየተጠቀሰች ያለችው ግን አጼ ኃ/ስላሴ ከቀዳማይ ወያኔ አመጽ በኋላ ትግራይን ለመቅጣትና ለማዳከም አስበው የወሰዱት እርምጃ መሰረት ያደረገው ነው። ታሪካዊ መሰረት የለውም፣ ምክንያት የሌለውና ለአጭር ጊዜ ብቻ የተደረገ በመሆኑ። እነዚህ ቦታዎች ወደ ወሎና ወደ ጎንደር (በነገራችን ላይ ወደ አማራም አይደልም)

አሜርገሪ ፔርሃም የተሰኘች እንግሊዛዊት ጸሓፍት፣ ከጣልያን መባረር በኋላ የኢትዮጵያን መንግስታዊ ታሪክ አጥንታ ብዙ ጽሁፎች ያሳተመች እውቅ ሰው ነች። በምኒሊክና በኃይለስላሴ በተለይም ከቀዳማይ ወያኔ በፊት የኢትዮጵያ አስተደድራዊ ክልል ምን ይመስል እንደነበረ በብዙ አስረጅና ካርታ አስደግፋ ያሳተመችው ጥናታዊ ጽሁፍ መጥቀሱ የማያወለዳ አስረጅ ይሆናል።

ይህ ከታች ያለው እድሜ ጠገብ ካርታ ከኢትዮጵያ አገር ግዛት ሚኒስቴር የተገኘ ነው። ከ5 አሰርት አመታት በፊት የኢትዮጵያ የውስጥ አስተደዳደር አከላል ይኽን ይመስል ነበር። ትግራይም ቁጥር 1 እና ቁጥር 2 ላይ እንደተመለከተው ምስራቅ ትግራይነ ምእራብ ትግራይ ተብላ ነበር። እዚህ ላይ በአማራነት የተጠቀሱት ሁለት ቦታዎች ብቻ ናቸው። ሰሜናዊ አማራና ማእከላዊ አማራ (3 እና 4) አሉ። የአማራ ብልጽግና አመራሮች ዛሬ ራሱ ተሰብስበው ያወጡት መግለጫ ስለ ወልቃይትና ራያ ጠቅሰዋል። ታሪክ፣ ህግ እና እውነት የማይደግፈው ጥያቄ እያነሱ ማራገብ የፖለቲካ ጥቅሙ ምን ሊሆን ይችላል?!

                

አስረጅ፡
ከታች ባሉት የተነባበሩት ብ1935 የነበረው የትግራይ ስፋትና የአሁኑን ለማነጻጸር ይረዳል። በአጼ ዮሃንስ ጊዜ ትግራይ ሃማሴንን ጨምሮ ብዙውን አሁን ያለው የኤርትራ ክፍል ታጠቃልል ነበረ። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ከነበሩት ጠቅላይ ግዛቶች ሁለቱ ሃብታሞች ተብለው በገብረህይወት ባይከዳኝ መጽሃፍ የተጠቀሱት ትግራይና ሸዋ ነበሩ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በቀንድ ከብት ብዛት ኢትዮጵያ ውስጥ ከነበሩት ግዛቶች ትግራይ አንደኛ ነበረች። ትግራይ ጦርነትና ጭቆና ርቋት አያውቅም። ትግልም እንዲሁ። ከወያኔ አመጽ በኋላ ኃይለስላሴ ትግራይ ላይ የጭቆናና የማቆርቆዝ ፖሊሲያቸውን አጠናክረው ገፉበት። ራያ ቆቦና ወልቃይት ከትግራይ የተወሰዱት በ1948 ነው። ትግራይ ለኢትዮጵያ ግዛታዊ ህልውና የከፈለችው ብዙ ሆኖ ሳለ፣ ራሷን ግን ከጊዜ ጊዜ እያሳነሰች የመጣች ክልል ናት። ህወሓት ስልጣን በያዘበት ዘመን የኢትዮጵያ ድህነት ከ42% ወደ 22% ሲወርድ፣ የትግራይ ድህነት 27% ላይ ይታያል። ይኽም ትግራይ ይህንን ጊዜ ተጠቅማ ለመቅደምና ለመበልጸግ አለመሞከሯን ያሳያል። ልክ የፈዴራል ስልጣን ላይ ያላት ተሳትፎ ወደ ዜሮ ከወረደ በኋላ ግን ጫናው ከግራም ከቀኝም ይበረታአ ጀመር። በዘመናት መካከል፣ ትግራይ ከውጭ ኃይሎች ከደረሰባት ጫና ይልቅ በኢትዮጵያ ገዢዎች የተበደለችው ሳይበዛ አይቀርም።   

እንግዲህ የወልቃይት ህዝብ የትግራይ ህዝብ ነው። ይህ ኣሁን ባለው ህገመንግስትና ኣከላለል ብቻ ሳይሆን ከጥንት ከጥዋቱ ጀምሮ ያለ እውነታ ነው። ይህንን ማንነት መቀየር ከፈለገ የሚወስነው ደግሞ የወልቃይት ህዝብ ብቻ ነው። ይኽ ውሳኔ የማንም ሌላ ህዝብ መብት ሊሆን ኣይችልም። ይኽ ስልጣንና መብት የጎንደርም አይደለም፣ የባህርዳርም አይደለም። የመቐለም አይደለም። የወልቃይት ህዝብ አሁን ያለውን ማንነት ማንም ሌላ ሰው ሊያስቀይረው እንደማይችል ሌላ ፍልጎት ካለውም ማንም ሊያቆመው ኣይችልም። በህግና በስርአት የሆነ እንደሆነ ግን መሰል ጥያቄዎች ኣሁን ባለው ህገመንግስት እንዴት እንደሚስተናገድ ህጋዊ ስርዓትና ኣሰራር ተበጅቶለታል። በዚህ መንገድ ጉዳዩን ለማየት ቀላል የመሆኑን ያህል በሌላ መንገድ ደግሞ ከባአድ ወይም የማይታሰብ ነው።

በህገመንግስቱ መሰረት ፌዴሬሹኑን ያቆሙት 9 ክልሎች ናቸው። የአማራ ክልል አመራሮችና ልሂቃን በህገመንግስቱ ላይ የሚያቀርቡት ትችትና ቅሬታ አሁን አሁን እየጎላ መጥቷል። ሲረቀቅና ሲጸድቅ አልነበርንበትም ይላሉ። ይኽ ግን ውሃ አይቋጥርም። የህገመንግስቱ አርቃቂ ኮሚሽን ከመሩት 15 ሰዎች 11 ከአማራ የተወከሉ ሆነው፣ በተለይ ደግሞ ሊቀመንበሩ ክቡር አቶ ክፍሌ ወዳጆና ምክትል ኮሚሽነሩ አቶ ዳዊት ዮሃንስ ሁለቱ የመሩት ሂደት፣ የአማራ ክልል (በቻርተሩ ዘመን ክልል 3) ላይ በህገ መንግስቱ ረቂቅ ይዘት ላይ የነበረውን የህዝብ ውይይት መድረኮች ያስተባበሩትና የመሩት አቶ ደመቀ መኮንን ሆነው ሳለ፣ አልነበርንበትም ማለት ይቻል እንደሆነ ለዚህ ጸሃፊ አስገራሚ ነው። በህገመንግስቱ የአንድ ወር ጉባኤ ላይ ከታደሙት ውስጥም በህዝብ ብዛት ልኬት የተወከሉ ጉባኤተኞች ነበሩ። በዚያ አጽዳቂ ጉባኤም ከኦሮሞ ህዝብ ተወካዮች ቀጥሎ በብዛት ደረጃ ከዚህ ክልል የመጡ ያክል የላከ ሌላ ክልል የለም። እጅግ አስደናቂው ደግሞ አሁን ያለው የአማራ ክልል ህገመንግስት ራሱ የፌዴራሉን ህገመንግስት መንትያ ቅጂ ነው።

እርግጥ ነው ለትግራይ ህዝብ ከራሱ በላይ የሚቀርበው ሌላ ህዝብ የለም። ከራሱ ቀጥሎ ግን፣ ለትግራይ ከአማራ ህዝብ በላይ አይደለም ከአማራው እኩልም የሚቀርበው ሌላ የፖለቲካ ማህበረሰብ አለ ብየ አላምንም። ለምሳሌ የኤርትራው ደጋማ ትግርኛ ተናጋሪ ክትግርኛ ተናጋሪው የትግራይ ህዝብ ጋር፣ ሳሆው ከኢሮብ ጋር፣ የመረብ-ማዶና መረብ-ወዲህ ኩናማዎች ወዘተ ቅርብ የባህል እና ቋንቋ ጥብቅ ዝምድና ወይም አንድነት ማየት እንችላለን። ግን በሌላ አገር ያሉ ህዝቦች እንደመሆናቸው ህጋዊም ፖለቲካዊም ዝምድናቸው ላይ ገደብ አለው። የትግራይና የአማራ ህዝቦች ግን እጅግ በብዙ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋም ጭምር የሚጋሩ፣ ከአንድ አይነት ግንደ ስልጣኔ የመጡ፣ ችግርም ድልም እንዲሁም በዘመናት መካከል መንግስታዊ አልጋም የተጋሩ፣ የወደፊት እጣ-ፈንታቸውም አንድ ላይ የተጋመዱ ህዝቦች ናቸው። በዚህ ዘመን ያሉ የአማራ ልሂቃን በተለይም ሚድያ ላይ የሚሰሩ አላዋቂዎች፣ ለአድማጭ-ተመልካቾቻቸው (ለአማራው) ትልቁ ጠላት አድረገው የሚያቀርቡት ትግራይና ትግራዋይ መሆኑ አስገራሚ ነው። በዚህ ምክንያት የትግራይ ህዝብ ብዙ ዋጋ ከፍሏል። የአማራ ህዝብም እንዲሁ። የኢትዮጵያን አገራዊ እግሮች እንዳይጸኑና አገሪቷ ወደ ብልጽግና እንዳትራመድ እጅ-ተወርች ካሰሯት እንቅፋቶች አንዱ ይኸኛው ትርክት ጎልቶ ይታያል። ግር የሚለው ደግሞ የአማራ ልሂቃን ስልጣን ፍለጋ በሚነጫነጩበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ስልጣን ላይም ሆነው ትግራይ ላይ ጥርስ የሚነክሱበት ምክንያት ነው። ውጤቱም ትግራይን፣ አማራን እና መላዋን ኢትዮጵያ ለከፍተኛ ኪሳራ የዳረገ ነው።

የሃብት፣ የባህልና የቢሮክራሲ የበላይነት ለማስጠበቅ ሲባል ትውልዶች ብዙ የውሸት ትርክቶች እንዲጋቱ አያሌ ጥረት ተደርገዋል። ከነዚያ አንዱ ስለኢትዮጵያዊነት የሚዘመረው ነው። የሚዘመረውን ያህል ኢትዮጵያን ወደ ስልጣኔና ዕድገት ለማስገባት የተደረገው ጥረት ከኢምንትም ያነሰ ነው። በተጨባጭ የኢትዮጵያን አገራዊ አንድነት አደጋ ላይ የጣደ፣ አገራችን በኋላ ቀርነትና ድንቁርና መጪዋን ያጨለመ፣ ሲሆን የአማራውን ጥቅም በማስጠበቅ ረገድ ያስመዘገበው ስኬት የለም። የሀገሪቷን አብሮነትና አንድነትም ከጊዜ ጊዜ እየተጎዳ ነው የመጣው። ለምሳሌ በአጼ ኃ/ስላሴ ጊዜ በፍጹም ዘውዳዊ አገዛዝ የሚዘወር አገራዊ ስርዓት ነበር። በደርግ ጊዜም የተወሰኑ የራስ ገዝ ሁኔታዎችና ለብሄር ብሄረሰቦች ህልውና በመስጠት ከዘውዳዊው የተለየ ወታደራዊ አገዛዝ ዘውዳዊውን ተክቶ ቀጠለ። ዝመኑና እድገቱ፣ ኢህአዴግ ለብሄር-ብሄረሰብና ህዝቦችን እንዲሁም ክልሎች ሰፋ ያለ ስልጣን በማረጋገጥ ያልተማከለ ፌዴራላዊ ስርዓት ማደራጀትን አስፈላጊ አደረገው። ከዘውድ ወደ ፌዴሬሽን መምጣት በጣም በጣም ብዙ ርቀት ነው። አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ አገራዊ ህልውናና ቀጣይነት ፖለቲካዊ ትምምን የራቀውና በሽፍጥ የተሞላ ጉዞ በማለፋችን ምክንያት ከኮንፌዴሬሽን ያነሰ አደረጃጀት አገሪቷን ሊያስቀጥል አይችልም የሚሉ አስተያየቶች እየተደመጡ ነው።

በመጨረሻም አንድ ጠቃሚ የሚመስለኝ ጽንሰ ሃሳብ ለማጋራት ልሞክር። በዚህ በዳታ ኢንዳስትሪ shared time, shared space algorithm የሚባል ጽንሰ ሃሳብ አለ። ቃላቱን ወደ ማህበራዊ ሁኔታ አምጥቼ ማስተዋወቅ እፈልጋለሁ። የሁለት ሰዎች ቅርርብና ዝምድና ወይም የሁለት ማህበረሰቦች ቅርርብና ዝምድና የሚገዛው ቀዳሚው ባህርይ ወይም ሊገዛው የሚገባው ቀዳሚው ባህርይ የሚጋሩት ጊዜና ምህዳር ነው። አመለካከትና እሴት በምንጋራው ጊዜና ስፍራ ማእቀፍ ሲታዩ ብቻ ናቸው ተጨባጭ ፋይዳ የሚላበሱት። በጊዚና በቦታ የሚገናኙ ሰዎች ግን ተመሳሳይ አስተሳሰብና እሴት እንኳ ባይኖራቸው የዝምድናቸው መደላድል እንደተነጠፈ ይታያል። ለምሳሌ ሁለት ሰዎች በተራራቀ ጊዜ ወይም በተራራቀ ቦታ ቢኖሩና በጣም የሚቀራረብ አመለካከት ወይም አስተሳሰብ ቢኖራቸው ግንኙነታቸው ወይም ዝምድናቸው የሌለ ያህል ወይም የላላ ይሆናል። በሌላ በኩል፣ ሁለት ወንድሞች ፍጹም የተለያየ እይታና አቋም ቢኖራቸው እንኳን ጊዜና ቦታ በመጋራታቸው ምክንያት ብቻ ቅርርባቸው ይቀጥላል። የእናትና ልጅ ፍቅርና ቅርበት ምንጩም ምናልባት ይህ ሊሆን ይችላል። በእርግዝና ወቅት ብቻ እንኳ ቢታሰብ ለ6500 ሰዓታት ያለማቋረጥ አንድ ጊዜና አንድ ቦታ አብረው ብቻ ሳይሆን ተጣብቀው ነው። ይኽ በሌላ ግንኙነት ላይ የሚታይ ፍጹማዊ የጊዜና ቦታ ግሪት አይደለም። የባህል፣ የታሪክ፣ የሃይማኖትና የመሳሰሉት አያያዥ ገመዶች እንዳሉ ሳንዘነጋ፣ አሁን ያሉት የአማራና የትግራይ ህዝቦች አንድ ዘመንና ኩታ ገጠም ቦታ የሚጋሩ ማህበረሰቦች ናቸው። ኩታ ገጠም ይባል እንጂ፣ ለአላማጣ ህዝብ ከዛላንበሳው ህዝብ በላይ የቆቦው ይቀርቧል። የቆቦው ህዝብ ከጎንደር ህዝብ ይልቅ የአላማጣው ይቀርቧል። አጼ ምኒልክና አጼ ዮሃንስ ከጊዜ አንጻር ሩቅ ናቸው። በመሆኑም ዓሁን ላለው የትግራይም ይሁን የአማራ ህዝብ በየበኩላቸው ላሉት አጼዎቹ ካለው ቅርበት በላይ መቀራረብ አለበት፣ ምክንያቱም አንድ ዘመን ስለሚጋራ። ለምሳሌ በትግራይ ክልል አደገኛ ጎርፍ፣ እሳት ወይም ሌላ ጠላት ቢያጋጥም በአካል ተገኝቶ እገዛ ማድረግ የሚችለው አጠገቡ ያለው የአማራ ህዝብ ነው። ለዚህም ነው ልሂቃኑና ፖለቲከኞቹ፣ በታሪክ እና በርስት ስም ሊያጋጩት ብዙ ጥረት ቢያደርጉም ህዝቡ ብዙም ያልሰማቸው። እነዚህ የማጋጨት ሙከራዎች፣ ተሞክረው ሲከሽፉ ሳይሆን ከመጀመሪያው እንዳይታሰቡና እንዳይሞከሩ ለማድረግ የሚያስችል ንቃት መገንባት የተራማጅ ልሂቃን የቤት ሥራ ሆኖ ይታያል። ሥርየት የሚገኘ

116 COMMENTS

 1. Howdy! This post could not be written any better! Reading this post reminds me of my old
  room mate! He always kept chatting about this. I will forward this post
  to him. Fairly certain he will have a good read.

  Thanks for sharing!

 2. Magnificent goods from you, man. I have understand your stuff previous
  to and you are just extremely wonderful. I really like what you have acquired
  here, really like what you are saying and the way in which you say it.
  You make it enjoyable and you still take care of to keep
  it smart. I can not wait to read far more from you. This is actually
  a wonderful web site.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here